Ethiopian Railways Corporation

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የትምህርትና ስልጠና መምሪያ ባዘጋጀው የስልጠና መርሃግብር፣ ለኮርፖሬሽኑ ሴት ሰራተኞች “Work-Life Balance and Empowering Women to Lead Change” በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጥቷል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮእህተ ከበደ፣ስልጠናው ሴት ሰራተኞች የሥራና የግል ሕይወታቸውን በሚገባ እንዲመሩ እንዲሁም የሥራ አፈጻጸማቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያስችል ተደማሪ እውቀትና ክህሎት ያስጨብጣቸዋል ብለዋል።

የኮርፖሬሽኑ የሥርዓተጾታ፣ሥነ-ምግባርና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ አይንአለም ወልደ ሥላሴ እንዳሉት የሴት ሰራተኞች ተቋማዊ የአመራርነት ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ በኮርፖሬሽኑ  በተጨባጭ እየታየ ነው። በዚህም እረገድ የኮርፖሬሽኑ ዋናሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ህሊና በላቸው ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅና የሚመሯቸውን ፕሮጀክቶች ሁሉ በላቀ ብቃት” በውጤት” በመቋጨት አርዓያ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሴት ሰራተኞች እንዲሁ ክህሎታቸውንና በራስ መተማመናቸውን በማጎልበት ወደ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪነትና የተቋም አመራርነት ደረጃ ለመድረስ በትጋት መሥራት እንዳለባቸው ኃላፊዋ በጽኑ አሳስበዋል።

ስልጠናውን የሰጡት የKalohe Consultancy ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ገነት ማሞ፣ የሥራና የግል ሕይወት ሚዛንን የመጠበቅ አስፈላጊነትን በማስመልከት ለተሳታፊዎች በእጅጉ ጠቃሚ  ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የስልጠናው ተሳታፊ ሴቶች በበኩላቸው፣  ኮርፖሬሽኑ በሀገር ደረጃ የባቡር ዘርፍ እድገትን ለማፋጠን እያደረገ ያለውን ውጤታማ ጥረት ብሎም የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንዲችልም ጭምር ስልጠናው  በግለሰብ ደረጃ ተጨማሪ አቅም ፈጥሮልናል ሲሉ ለኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ሰጥተዋል።

ከኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት !

 

ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ ፤

ፌስቡክ፡  https://www.facebook.com/…/Ethiopian-Railways…/
ቴሌግራም:  https://t.me/EthiopianRailwaysCorporati
ድረ  ገፃችንንም ይጎብኙ:  www.erc.gov.et