Ethiopian Railways Corporation

ኮርፖሬሽኑ ISO 9001፣ ISO 14001 እና ISO 45001 መስፈርቶችን አቀናጅቶ ለመተግበር የሚረዳ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል፡፡

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ — የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ የISO/IMS የእውቅና ሰርተፊኬት ለማግኘት በትኩረት እየሰራ የሚገኝ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ህሊና በላቸው ገለጹ።

“በአጭር ጊዜ የISO/IMS ዓለም አቀፍ የደረጃ ሰርተፊኬት ለማግኘት በትኩረት እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ ኢንጂነር ህሊና ተናግረዋል።

በኮርፖሬሽኑ የISO/IMS ዓለም አቀፍ የሥራ ላይ መመሪያዎችን በተሻለ ለማስፈጸም እንዲቻል  ከሁሉም የሥራ ክፍሎችና ፕሮጀክቶች የተወጣጡ ኮሚቴዎች ለማኔጅመንት አሁናዊ የሥራ አፈጻጸማቸውን በዝርዝር በማቅረብ አስገምግመዋል።

በኮርፖሬሽኑ እየተተገበረ ያለው የተቀናጀ የአስተዳደር ሥርዓት የISO 9001 የጥራት አስተዳደር፣ ISO 14001 የአካባቢ አስተዳደር እና ISO 45001 የሥራ ቦታ ጤናና ደህንነት መስፈርቶችን በአንድ ሥርዓት ውስጥ ለማቀናጀት ያለመ ነው። ኮርፖሬሽኑ ይህንን ሥርዓት በሁሉም የሥራ ክፍሎችና ፕሮጀክቶች ላይ በመተግበር ለሰርተፊኬት ሂደቱ ዝግጅት እያደረገ ነው።

ኢንጂነር ህሊና በላቸው  እንዳሉት ፣ ዘመናዊ የባቡር መጓጓዣ ሥርዓት ሰዎችንና ዕቃዎችን ከማጓጓዝ ባሻገር የጥራት፣ የደህንነት፣ የአካባቢ ጥበቃና የዘላቂነት ኃላፊነቶችንም በተቀናጀ መልኩ መወጣት ይጠበቅበታል።

በኮርፖሬሽኑ የሥራ ቦታ ደህንነትን መጠበቅ፣ አካባቢን መንከባከብ፣ አስተማማኝና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲሁም የደንበኞችን፣ የሠራተኞችን፣ የአጋሮችንና የማኅበረሰቡን እምነት ማጠናከር የሁሉም የጋራ ኃላፊነት መሆኑ በሥራ አፈጻጸም ግምገማው ላይ ተጠቁሟል ።

የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራሮች የፖሊሲውን ተግባራዊነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ሲኖርባቸው፣ ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በተቀናጀው የአስተዳደር ሥርዓት ውጤታማነትና ቀጣይ መሻሻል ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠይቀዋል።

የኮርፖሬሽኑ የISO/IMS ቁርጠኝነት የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው የዕድገት እንቅስቃሴ፣ የቀጠናዊ  ንግድና የለውጥ ኃይል ለማድረግ በሀገር ደረጃ ከተቀመጠው ራዕይ ጋር የሚጣጣም ነውም ተብሏል ።

ከኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት !

ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ ፤

ፌስቡክ፡  https://www.facebook.com/…/Ethiopian-Railways…/
ቴሌግራም:  https://t.me/EthiopianRailwaysCorporati
ድረ  ገፃችንንም ይጎብኙ:  www.erc.gov.et