Ethiopian Railways Corporation

ቋንቋ

ኀዳር 17, 2016 ዓ.ም ( ኢምባኮ)
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በኮርፖሬሽኑ የ2016 ሩብ በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ዙሪያ ከማኔጅመንት አባላት ጋር ኀዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል ውይይት አካሂዷል

በውይይቱ መክፈቻ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢ/ር ጌቱ ግዛው እንደገለጹት የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የተቋሙን አፈጻጸም ትኩረት ሰጥቶ በመገምገም ጠንካራ አፈጻጸሞችን ለማስቀጠል እና የታዩ ክፍተቶችን ለማመላከት በመድረኩ በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ኢያሱ ሳላ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ባደረጉት የመግቢያ ንግግር የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባለፉት ዓመታት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት የመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርግቶ ወደ አገልግሎት ማስገባቱን አስታውሰው አሁንም በርካታ የሥራ እቅዶችን ለማሳካት እያደረገ ያለው የሥራ እንቅስቃሴ በጠንካራ ጐን የሚታይ መሆኑን ገልጸው በውይይቱ ወቅት ከሚነሱ ጉዳዮች አንጻር ቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የውይይቱ ዋና ዓላማ በተቋሙ የ2016 ዋና ዋና ግብ ተኮር ተግባራት እቅዶችና የሩብ አመት እቅድ አፈጻፀምና ሌሎች ወሳኝ የሆኑ ትኩረት የሚሹ የተቋሙ ጉዳዮች ላይ ለመምከርና ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ አመታት የሚመራበት ፍኖተ ካርታ ላይ ያተኮረ ውይይት ለማድረግ መሆኑን ተገልጿል፡፡

ለቋሚ ኮሚቴው አባላት የኮርፖሬሽኑ ም/ሥራ አስፈጻሚዎች ኢ/ር ጌቱ ግዛው እና ኢ/ር ስለሺ ካሳ እንዲሁም አቶ ሰው መልካም ሙሉጌታ የኮርፖሬሽኑ የምህንድስና ግዥ እና ጥገና መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት አላማ በመነሳት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ አዳዲስ ቢዚነስ ዩኒቶችና ፕሮጀክቶችን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ የተሰሩ ስራዎች፣ የባቡር መስመር የግንባታ እቅዶችና ተያያዥ ልማቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም በዘርፉ ከመንግስት የሚፈለግ ድጋፍ ምን ይመስላል? የሚሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባላትም በቀረበው የሩብ አመት እቅድ አፈፃፀምና ፍኖተ ካርታ ላይ ያላቸውን ሃሳብና ጥያቄዎች አንስተው ከሚመለከታቸው የኮርፖሬሽኑ የማኔጅመንት አባላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በውይይቱ ማጠናቀቂያም የምክር ቤት አባላቱ በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው ጉብኝት አካሂደዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት ተገኝተው የስራ እንቅስቃሴዎችን የተመለከቱ ሲሆን በተለይ በተቋሙ የተመለከቱት የህጻናት ማቆያ በዘመናዊ መልክ የተደራጀ መሆኑ ያስደሰታቸው መሆኑን ጠቅሰው ከተደረገላቸው ገለጻ በመነሳት ወላጆች ልጆቻቸው በማዕከሉ እንክብካቤ ስለሚደረግላቸው ሙሉ ሀሳባቸውና አቅማቸውን ስራ ላይ በማዋል ውጤታማ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ ለሰራተኛውም ሆነ ለተቋሙ ትልቅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ የሚኖረው በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ በዚህ ረገድ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ያደረገው እንቅስቃሴ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተከበሩ ዘውዱ ታደሰ (ዶ/ር) የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በውይይቱ ማጠቃለያ ባደረጉት ንግግር በቀረበው ገለጻ እና በጉብኝቱ አባላቱ ስለ ኮርፖሬሽኑ የሥራ እንቅስቃሴ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡ አክለውም ኮርፖሬሽኑ ጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በቀጣይ ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

 

 



Leave a Reply