Ethiopian Railways Corporation

ህዳር 27/2016ዓ.ም ኢምባኮ
የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎችና አጠቃላይ ሰራተኞች በኮርፖሬሽኑ ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ላይ ህዳር 27/2016 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ ውይይት አካሄዱ፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው ገለፃ ያደረጉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ህሊና በላቸው (ኢ/ር) ኮርፖሬሽኑ በለውጥ ሂደት ላይ በመሆኑ ሰራተኛው ለሚፈለግበት ለውጥ በመዘጋጀት እራሱን የለውጡ አካል አድርጎ በመስራት ተቋሙ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል በመተጋገዝ የራሱን አሻራ ማሳረፍ እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል፡፡

የውይይቱ ዓላማ በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ምን ይመስላል? እስካሁን በተሰሩ የቢዝነስ ዩኒት ስራዎች የተገኘ ውጤት መሻሻልና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ምንድናቸው? ሰራተኛው ያለው አጠቃላይ ግንዛቤ ምን ይመስላል? የሚሉ ጉዳዮችን ለማየት መሆኑ ተገልጸዋል፡፡

የባቡር ፕሮጀክት ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ በአዋጅ ከተቋቋመበት የባቡር መሰረተ ልማት መገንባት፣ የመንገደኞችና የጭነት አገልግሎት የመስጠት ተልዕኮው በተጨማሪ የባቡር ዘርፉን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችሉ ተያያዥ ተግባራትን በማከናወን የተለያዩ የቢዝነስ ዩኒት ስራዎች ለመስራት በሂደት ላይ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገልፀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፉ ተመራጭ፣ የጎላ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክት፣ በደንበኞቹ ተመራጭ ለሰራተኞቹም ምቹ የስራ ቦታ ያለው ሆኖ እንዲቀጥል እያንዳንዱ ሰራተኛ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ የባቡር ዘርፉ ለቀጣይ አስራ አምስት ዓመታት የሚመራበት የባቡር ፍኖተ ካርታ፣ የኮርፖሬሽኑ የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ፣ የለውጥ አመራር፡ የመልቲ ሞዳል፣ እና የቢዝነስ ዩኒት ሥራዎች አፈጻጸም በዝርዝር የሚቀርቡ ርዕሰ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

 

 

 

 



Leave a Reply