Ethiopian Railways Corporation

ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም፣ (ኢምባኮ)

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስር ለሚገኙ አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች የገና በዓልን አስመልክቶ ታህሳስ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በወረዳው ቅጥር ግቢ በመገኘት የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር አካሄደ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ ለሚሹ አካላት ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኝ ሲሆን በዚህም ታህሳስ 28 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረውን የገና በዓል በማስመልከት በወረዳው ለሚገኙ 148 ለሚሆኑ አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች ለእያንዳንዳቸው የአምስት ሊትር ዘይት እና 10 ኪሎ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል፡፡

በማዕድ ማጋራት ሥነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኮርፖሬሽኑ የስርዓተ ፆታና ማህበራዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቡድን መሪ ወ/ሮ ሰዓዳ ጀማል እንደገለፁት፤ ኮርፖሬሽኑ ተልዕኮውን ለማሳካት ከባቡር ግንባታ ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት በሌሎች ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የራሱን አሻራ እያሳረፈ መሆኑን ገልጸው በዚህም መሠረት በወረዳው የሚገኙ አቅመ ደካሞችን ለመደገፍና ኮርፖሬሽኑም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ግብአቶቹን ያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ለሜሳ ነገሪ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ዋና ሥራ አስፈፃሚ በበኩላቸው “በአሉን ስናከብር የሰው ተኮርና የአብሮነት እሳቤን በተግባር የምናረጋግጥበት ነው” በማለት የገለጹ ሲሆን የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለወረዳው አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የማዕድ ማጋራት ማካሄድ በመቻሉ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ይህ አርዓያነት ያለው ተግባር ወደፊትም በሌሎች አካላትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በማዕድ ማጋራቱ ኘሮግራም ላይ ኮርፖሬሽኑ በቋሚነት ድጋፍ የሚያደርግላቸው ቤተሰቦችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 



Leave a Reply