- August 16, 2024
- Posted by: Tigist desalgn
- Category: ዜና
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ ገመገመ፡፡
የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማው የኦፕሬሽን፣ የፋይናንስ፣ የኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ የፕሮጀክት እና የሪፎርም ግቦች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ሲሆን ፣ ድርጅቱ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅዱ ከ2013 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ከሚቆይና ከተዘጋጀው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ፣ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ከነበራቸው ዕቅድ አፈጻም ፣ድርጅቶቹ ካሉበት ነባራዊ ሁኔታና ሌሎች መመዘኛ መስፈርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የራስ ኃይል የቢዝነስ ዩኒቶችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ፈቃድ ወስዶ ወደተግባር መግባት መቻሉ ፣በውስጥ አቅም የሰው ሀብት ለማልማት ያከናወናቸው ተግባራት በበጎ ጎን የታዩ ተግባራት ናቸው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው ልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተግባራት የብር 79.8 ሚሊዮን ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ በራስ ኃይል ሥራዎችን ለማከናወን ባቀደው ዕቅድ መሰረት የብር 6.6 ሚሊዮን ወጪ ማዳን ችሏል፡፡ ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ የቢዝነስ ሀሳቦችን አመንጭቶ ወደተግባር በማስገባት አማራጭ የሥራ መስኮችን ለመፍጠር ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች እንደነበሩ በግምገማው ታይተዋል፡፡
ግምገማውን የመሩት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ያከናወቸውን ተግባራት በማመስገንና እንደዜጋ ለማገልገል የተደረገውን አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም መሻሻል ያለባቸውን ተግባራት በመጠቆም ኮርፖሬሽኑ በሀገር ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረት አድርጐ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
===##==
ምንጭ- የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር