- December 13, 2024
- Posted by: Tigist desalgn
- Category: ዜና
ታኀሣሥ 3/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና በጣሊያን COIPA ካፒታል መካከል የመሠረተ ልማት ኘሮጀክቶች እድገትና ትስስር ለማጠናከር እንዲረዳ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የቢዝነስ ዴቨሎኘመንት ስትራተጂ ዘርፍ ም/ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ግዛው (ኢ/ር) እና የCOIPA ካፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ Vito Favorito Sciammarella (ዶ/ር) ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ የባቡር መስመርና የሎጅስቲክስ አቅምን ለማጠናከር የሚረዳ ነው፡፡
ስምምነት የተደረሰባቸው በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ላይ ከሚገኙት የሎጅስቲክስ ማዕከል ኘሮጀክቶች መካከል የወጪ ገቢ ጭነት ለማስተናገድ የሚያስችል የእንዶዴ ሎጅስቲክስ ማዕከል፣የሞጆ ደረቅ ወደብና የመልቲ ሞዳል ማዕከል፣ የአዳማ ከተማ የትራንስፖርት ተርሚናል እና የንግድና የመኖሪያ ቦታዎች፣የድሬዳዋ መልካ ጀብዱ የኢንዱስትሪና የሎጅስቲክስ ማዕከል ይገኙበታል፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ ሊገነባ የታሰበው በዘርፉ የሚስተዋለውን የሰው ኃይል እጥረት በመፍታት በአመት ከ3000 በላይ ሰልጣኞችን በመቀበል የማሰልጠን አቅም የሚኖረው የባቡር አካዳሚ የልህቀት ማዕከል ኘሮጀክት ሌላው የስምምነቱ አካል ነው፡፡
መስመሩን ከጅቡቲ ጋር በማገናኘት ማዕድናትን ለማጓጓዝ የሚረዳው የኦጋዴን—ጅቡቲ ወደብ የባቡር መስመር ኘሮጀክት በስምምነት ማዕቀፉ የተካተተ ነው፡፡
በተጨማሪም የኮርፖሬሽኑን የግንባታና የአማካሪነት ቢዝነስ ዩኒት እንደገና በማዋቀር በምስራቅ አፍሪካ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመስራት የሚያስችል “ኢትዮ—ባቡር ኮንስትራክሽን እና አማካሪ ግሩኘ” ወደሚል ስያሜ ማሸጋገር የሚሉት በስምምነቱ ላይ የተጠቀሱ ናቸው፡፡
COIPA በቀጣዮቹ አመታት የጣሊያንን የአፍሪካ ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ እና ለመተባበር የተጀመረውን መርሃ ግብር በ“Mattei Plan for Africa” ውስጥ የተገለጹትን ውጥኖችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ ያደርጋል፡፡
የስምምነቱ ዓላማ COIPA ካፒታል ትልልቅ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን በቴክኒክ እና በማማከር እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ያለውን ሰፊ ልምድ በመጠቀም ከኮርፖሬሽኑ ጋር በንግድ ትብብር ተቀናጅቶ በመስራት የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣የፋይናንስ አቅምን በማጎልበት ሀገራዊ የባቡር መስመሩን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ነው፡፡
ስምምነቱ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በዘርፉ ሰፊ የስልጠና እድሎች በመፍጠር ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የቢዝነስ ዴቨሎኘመንት ስትራተጂ ዘርፍ ም/ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ግዛው (ኢ/ር) ስምምነቱ የሀገራችንን መሰረተ ልማት ዘመናዊ ከማድረግና ተልዕኮውን ለማሳካት የሚያስችል ስትራተጂክ ምዕራፍ የሚወክል ከመሆኑ ባሻገር በዘርፉ አለም አቀፍ ልምዶችን በመቀመር ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያረጋግጥና ደረጃቸውን የጠበቁ የሎጅስቲክስ እና የባቡር መስመሮችን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የCOIPA ካፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ Vito Favorito Sciammarella (ዶ/ር) በበኩላቸው ከኮርፖሬሽኑ ጋር በአጋርነት ለመስራት በዘርፉ የካባተ ልምድ እና የፋይናንስ አማራጮችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ግዙፍ መሠረተ ልማት ግንባታዎች በመደገፍ በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡