Ethiopian Railways Corporation

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከፊዛ ኤሊክሰር ኢንፍራስትራክቸር ፕራይቬት ሊሚትድ ጋር የሁለቱን ተቋማት የፋይናንስና የቴክኒክ አቅም በማጣመር የጋራ ልማትና የንግድ ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት የሚያስችል የስትራቴጂክ ማዕቀፍ ስምምነት (Master Framework Agreement) ተፈራርሟል ።

ስምምነቱ የኮርፖሬሽኑን ሀብቶች በማልማት አዳዲስ የገቢ ምንጮችን ለመፍጠር፣ የፋይናንስና የቴክኒክ አቅምን ለማጠናከር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማመቻቸት እና በባቡርና በኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ዘርፎች የንግድ ዕድሎችን ለማስፋፋት ያለመ ነው።

የኮርፖሬሽኑ የባቡር መሠረተ ልማት ዘርፍ ም/ሥራ አስፈፃሚ ኢ/ር ስለሺ ካሳ እንደገለጹት፣ ስምምነቱ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችንና የኮርፖሬሽኑን የፋይናንስ ዘላቂነት በማጎልበት የሥራ ዕድልን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የሀገር ውስጥ ምርትንና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ አስተዋፅዖ ያደርጋል ብለዋል ።

የፊዛ ኤሊክሰር ኢንፍራስትራክቸር ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ሙሐመድ ፋሩጉዲን በበኩላቸው፣ ስምምነቱ ፋይናንስ ለማሰባሰብ፣ የአቅም ግንባታን ለማጠናከር እና የሁለቱን ተቋማት ልምድና አቅም በማጣመር የልማትና የንግድ ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት መሠረት እንደሚጥል አስረድተዋል ።

የስምምነቱ ዋና የትኩረት መስኮች የኮምቦልቻ ወርክሾፕን በማልማት የባቡር ጥገና፣ የመለዋወጫ እቃዎችና የባቡር አካላት ማምረቻ ማዕከል ማቋቋም፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርን በዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ቲኬቲንግ ሥርዓት ማሻሻል፣ ተጨማሪ ባቡሮችን ማቅረብ፣ የኤሌክትሪክ፣ የሲግናልና የኮሙኒኬሽን ሥርዓቶች ማዘመንን የሚያካትት ነው።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ በተመረጡ ቦታዎች የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ቻርጂንግ ጣቢያዎችን ማቋቋም፣ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን ማስገባት፣ የአገር ውስጥ ማምረትን ማጠናከር እና በባቡርና በኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ዘርፍ የሚፈጠሩ የንግድ ዕድሎችን ማስፋፋት የስምምነቱ  አካል እንዲሆን ተደርጓል ።

የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንትና ማርኬቲንግ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ስዩም ገዝሙ እንዳስታወቁት፣ ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት የአዋጭነትና የቴክኒክ ጥናት እንዲሁም የፋይናንስ ዝግጅት ይከናወናል። በመቀጠልም ፕሮጀክቶቹን ለመተግበር ልዩ የፕሮጀክት አካላት (Special Purpose Vehicles) የሚቋቋም መሆኑን አመላክተዋል ።

ስምምነቱ የኢትዮጵያን የባቡርና የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ዘርፍ ለማዘመን፣ የአገር ውስጥ ማምረትን ለማሳደግ እና ዘላቂ የልማትና የንግድ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያግዝ የትብብር መሠረት ይፈጥራልም ተብሏል ።

ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ ፤

ፌስቡክ፡  https://www.facebook.com/…/Ethiopian-Railways…/
ቴሌግራም:  https://t.me/EthiopianRailwaysCorporati
ድረ  ገፃችንንም ይጎብኙ:  www.erc.gov.et