Ethiopian Railways Corporation

የስልጠናውን መጀመር አስመልክተው የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ  ጌቱ ግዛው(ኢ/ር) ባደረጉት ንግግር  የስልጠናው ዋና አላማ የኮርፖሬሽኑን አሰራር ዘመናዊ በማድረግ ከወረቀት ነፃ የሆነ ፈጣን የመረጃ አያያዝ እና ልውውጥ ስርዓትን ለማስፈን መሆኑን ገልፀው ሰልጣኞች ለስልጠናው ትኩረት ሰጥተው መከታተል እንዳለባቸው እና ከሰለጠኑ በኋላ በየስራ ክፍላቸው ያሉ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ወደ ትግበራ ስርአት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የአይ.ሲቲ እና ሰነድ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ ተስፋዬ እንደገለጹት የManagement Information System (MIS) ያለውን ውስን ሀብት የሰው ሀይልም ሆነ የቁሳቁስ አቅርቦት በማሰባሰብ ጥራትን እና ፍጥነት ያለው አሰራር የሚያረጋግጥ ሲሆን ጥናቱ ከተጀመረ ከሰባት አመት በላይ ቢሆንም  በተለያዩ ምክንያቶች ባለመጠናቀቁ ተግባራዊ ሳይደረግ መቆየቱን ጠቅሰው ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል የሀርድ ዌር ተከላ አስፈላጊ በመሆኑ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ትግበራ ለማስገባት በቅድሚያ ለባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ ሶስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን እነሱም፡- የሶፍት ዌር፣ የኔትወርክ ዝርጋታ እና ዘመናዊ የዳታ(መረጃ) ማዕከል ማቋቋም ናቸው፡፡ ለኘሮጀክቱ በአዲስ መልክ  የውል ማሻሻያ በማድረግ  ለስራ የሚመጥኑ የኔትወርክ መሳሪያዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለመጀመር እቅድ ተይዞ ስልጠናው መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

ስልጠናው ተጠናቆ አሰራሩ ተግባራዊ ሲደረግ ፈጣንና ዘመናዊ አሰራርን በማስፈን መረጃን በአግባቡ ለመያዝ፤ የወረቀት ስራዎችን በመቀነስ ፍጥነት ፣ጥራት እና ወጪ ቆጣቢ አሰራር እንዲኖር የሚረዳ መሆኑን፣ በዚህም ተቋማዊ አሰራሩን ወጥነት ያለው እና የጊዜ እና የሀብት ብክነትን ለማስቀረት የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ስልጠናው በዋናነት ትኩረት የሚደረግባቸው ዘርፎች በሰው ኃይል፣ በግዢ ፣ በንብረት አያያዝ ፣ፋይናንስ እና ኘላኒንግ ላይ መሆኑን ጠቅሰው ስልጠናውና የፕሮጀክት ትግበራዉ በ9 ሞጁሎች የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡



Leave a Reply