Ethiopian Railways Corporation

ኀዳር 24/2017 ዓ.ም (ኢምባኮ)
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ሀጂ አወል አርባ፣የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ህሊና በላቸው (ኢ/ር)፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ክቡር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ፣ የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማኀበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) እና የኮርፖሬሽኑ የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት እየተገነባ ያለው የአዋሽ ነዳጅ ዴፖ ኘሮጀክት ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ኘሮጀክቱ በተሽከርካሪ ብቻ የሚመጣውን ነዳጅ በባቡር ትራንስፖርት አማራጭ እንዲገባ በማድረግና የትራፊክ መጨናነቅን በመቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና የአዲስ አበባ – ጅቡቲ የባቡር መስመርን ከአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ጋር ከማገናኘት አንጻር ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለው የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ህሊና በላቸው (ኢ/ር) ገልጸዋል፡፡ የሥራ ኃላፊዎቹም እየተገነባ ያለውን ኘሮጀክት የደረሰበትን ደረጃ ተዘዋውረው ጐብኝተዋል፡፡

በወቅቱም የአዋሽ–ወልዲያ–ሃራ ገበያ የባቡር መስመር በሚያልፍባቸው የክልሉ አካባቢዎች እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች እና የጥበቃ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት የተካሄደ ሲሆን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በቀጣይ ከወረዳ እና የዞን መስተዳድሮች ጋር ውይይት እንደሚካሄድ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በማጠቃለያውም ክቡር ሀጂ አወል አርባ በባቡር መስመሩ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቀነስ ተቀራርቦ መስራቱ አስፈላጊነቱ የጎላ መሆኑን ገልጸው በውይይቱ የተነሱ ነጥቦች ላይ ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ ክልሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ ፤
ድረ  ገፃችንንም ይጎብኙ:  www.erc.gov.et

 

 

 

 

 

 



Leave a Reply