Ethiopian Railways Corporation

ዜና ሀተታ
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር ካሉ የልማት ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ ዋነኛ ተልዕኮው የባቡር ትራንስፖርት መሠረተ ልማትን መዘርጋት እና የመንገደኞች እና የጭነት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቶችንና ተዛማጅ ሥራዎችን ማከናወን እንደሆነ የኮርፖሬሽኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አደረጃጀት ከግንባታና ዲዛይን እንዲሁም ከባቡር ኦፕሬሽን ሥራዎች ጋር ተያያዥ የሆኑ የተለያዩ ቢዝነስ ዩኒቶችን በማደራጀት የገቢ ማመንጫና የቢዝነስ ሥራዎችን ለማከናወን በማቀድ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ፋይናንስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ አስራት እንደሚገልፁት ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ በለውጥ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ከባቡር መሠረተ ልማት ጎን ለጎን ተያያዥ ሥራዎችን ለመከወን የተለያዩ የሥራ አማራጮችን በማቋቋም በመሠረተ ልማት፣ በመንገድ፣ በህንፃና በተለያዩ የማማከርና የግንባታ ሥራዎች ፈቃድ አግኝቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

የዘርፉን የሰው ሃይል በስልጠናና በቴክኖሎጂ ከማብቃት አኳያም አያት አካባቢ የባቡር አካዳሚ ኢንስቲትዩት አቋቁሞ እየሠራ ይገኛል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በተግባር የተፈተኑ ትልልቅ ባለሙያዎች እንዳሉት የገለፁት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ በውጪ ሀገራት ሰልጥነው መምጣታቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ ባለሙያዎች ለሌሎች አጎራባች ሀገራት የሚተርፉ መሆናቸውን ጠቁመው ምናልባት በአፍሪካ የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ባቡር የኢትዮ- ጅቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እየሠሩ ያሉ ባለሙያዎችም መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ፣ እነዚህ ባለሙያዎች ለሌሎች ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉበት ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ ይገኛል፡፡ አያት አካዳሚ ነባርና በጣም ዘመናዊ አካዳሚ ነው፡፡ ሁሉንም ያሟላ በኮሌጅ ደረጃ ያለ አካዳሚ ነው፡፡ አካዳሚው ከኢትዮጵያ አልፎ የሌሎች ሀገራት ሠልጣኞችን ተቀብሎ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉና ሀገራችንም ከዛ በሚገኘው ምንዛሬ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ከቻይና ኮሌጆች ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ማድረጉን ገልፀው በሥርዓተ ትምህርት ቀረፃው ላይም እገዛ እንዳደረጉ አስረድተዋል፡፡ ለባለሙያዎች ሥልጠናም የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በቀጣይ አመትም ተማሪዎችን ተቀብሎ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እንደታቀደም ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቢሾፍቱ ላይ ግዙፍ አካዳሚ ለመገንባት 60ሺህ ካሬ ሜትር መሬት መረከቡን ገልፀው በባቡር ዘርፉ ቀዳሚ የሆነችውን ሀገራችንን የሚመጥን እንዲሆን መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

 

በኮርፖሬሽኑ የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ኢንጂነር ጌቱ ግዛው በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ከዋነኛ ተልዕኮዎቹ ባሻገር ተዛማጅ ሥራዎችን በመሥራት ገንዘብ ለማመንጨት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከለውጡ በፊት ለተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለማስፈፀም ብድር ሲጠቀም እንደነበር ገልፀው፣ አዋጭ ስላልሆነና ለተቋሙም የብድር ጫና ከማስከተሉ አኳያ ሌሎች የገንዘብ ማመንጫ አማራጭ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም ከ2014 ጀምሮ ኮርፖሬት ፋይናንስና የመንገድ ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች የሚሉ የፋይናንስ አማራጮችን ይዞ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ዘርፍ በኮንስትራክሽን ላይ ያተኮሩ ስምንት የሚሆኑ ቢዝነስ ዩኒቶችን ማቋቋሙን ገልፀዋል፡፡ በመንገድ ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ዘርፍ ደግሞ የመንገድ፣ የባቡርና የህንፃ ቁጥጥር ሥራዎችን እንዲሁም የምህንድስና ላቦራቶሪና ተያያዥ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑን ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታን ጨምሮ ጥናታቸው የተጠናቀቀ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልፀው በኮምቦልቻ ቅርንጫፍ አራት ድልድዮችን እንዲሁም የባሌ ጋሲያ ፕሮጀክትን ወስዶ እየሠራ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የባቡር አካላትን የሚያመርትና ጥገና የሚያደርግ ወርክሾፕ በሞጆ ከተማ ለማቋቋም እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ምየኮርፖሬሽኑ ተዛማጅ ሥራዎችን የመሥራት ውጥን
— March 22, 2025 comments off

 

 

ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ ፤
ድረ  ገፃችንንም ይጎብኙ:  www.erc.gov.et

 

 

 

 

 

 

 



Leave a Reply