- October 8, 2025
- Posted by: Tigist desalgn
- Category: ዜና

መስከረም 28/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የኢኮ ቱሪዝም አገልግሎት ለመስጠት በራስ አቅም እየተዘረጋ ያለው የባቡር መስመር ፕሮጀክት ከፍተኛ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡ ይህንን የባቡር መስመር በራስ አቅም መገንባት መቻል ሀገራችን እያስመዘገበችው ያለውን ሁለገብ እድገት ማሳያ እና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ውጤት ነው፡፡
የኢኮ ቱሪዝም የባቡር መስመር ዝርጋታ በሀገራችን የባቡር ኢንዱስትሪ ውስጥ በራስ መተማመን መንፈስ፣ የቴክኒክ ልህቀት፣ የፈጠራ ነፃነት እና ሀገራዊ አቅም ግንባታ ላይ ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በማሳየት በባቡር ኢንዱስትሪው ላይ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲመዘገብ እድል ፈጥሯል፡፡ ይህ የቴክኖጂ ሽግግር ከዚህ በፊት ለውጭ ሀገር ባለሙያዎች ሲከፈል የነበረውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ አስቀርቷል፡፡
ይህ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢኮ ቱሪዝምን ያማከለ የባቡር መስመር ከዚህ ቀደም ከታዩት የባቡር መሠረተ ልማቶች የሚለየው ከፕሮጀክት ማናጅመንት እስከ ገንቢ የባቡር ቴክኒሻኖች ድረስ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የባቡር ባለሙያዎች የሚመራ መሆኑ ነው፡፡ እያንዳንዱ የግንባታ ምዕራፍ የሀገራችን በራስ አቅም የመስራት ጥንካሬ፣ ፈጠራ እንዲሁም የኮርፖሬሽኑን የረጅም ጊዜ ኢትዮጵያውያን የባቡር መሃነዲሶችና ቴክኒሻኖች በግንባታ እና የኦፕሬሽን አመራር የማብቃት ስራ ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተሰራ መሆኑን ያረጋገጠ ነው፡፡
በአፍሪካ የኢኮ የቱሪዝም የባቡር አገልግሎት ያላቸው ሀገራት ጥቂት ሲሆኑ ይህ የኢኮ ቱሪዝም የባቡር መስመር በሀገራችንም ሆነ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት አዲስ እድገትን የሚያመላክት ሲሆን ይህም ሀገራችን እየተገበረችው ያለው ሰፊ የቱሪዝም ልማት ላይ በአህጉራችን ጎብኚዎችን መሰረት ያደረገ የባቡር ሀዲድ ግንባታን በማከናወን ግንባር ቀደም ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ ያደርጋታል፡፡
ፕሮጀክቱ አቅምን በማሳደግ እና በፈጣን የፕሮጀክት አፈፃፀም ሂደት በኮርፖሬሽኑ ውስጥ የ24/7 የስራ ባህል ልምድን ከማዳበሩም ባለፈ ወደ ፕሮጀክቱ ጥቂት ልምድ ያላቸውን መሐንዲሶች እና ቴክኒሻኖች ብቻ በማሰማራት በፕሮጀክቱ አከባቢ ያሉ በርካታ ወጣቶችን በዘመናዊ ባቡር መስመር ግንባታ ላይ እንዲሰለጥኑ በማድረግ እና በግንባታው ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩ በማድረግ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
የኢኮ ቱሪዝም የባቡር ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ የዝርጋታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የባቡር መስመር ዝርጋታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ጎብኝዎች የታሪካዊውን ቦታ ተፈጠሯዊ መልክዓ ምድር ለመጎበኘት ከማስቻሉም በተጨማሪ ለወደፈት አከባቢውን ከአገሪቱ የባቡር ኔትወርክ ጋር በማገናኘት የባቡርን ተደራሽነት ማሳደግ፣ በአከባቢው ያሉ የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅ በሀገራችን ቱሪዝም እድገት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
ፕሮጀክቱ ከባቡር መስመር ዝርጋታ ባሻገር ለመጀመሪያ ጊዜ የመንገደኞች ባቡር (passenger train coach) ያመረተ ሲሆን ይህም ኮርፖሬሽኑ በሀገር ዉስጥ የተመረተ የቱሪዝም ባቡር ለመጀመርያ ጊዜ አገልገሎት ላይ ያዋለበት ፕሮጀክት ነው።
ተቋማችን ከሀገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች ጋር በመተባበር የባቡር መለዋወጫዎችን በአገር ውስጥ ለማምረት እና ከአለማቀፍ ታዋቂ የባቡር አምራች ድርጅቶች ጋር በመሆን የባቡር ማምረቻ እና መገጣጠሚያ ማዕከል በማቋቋም የውጭ ጥገኝነትን በመቀነስ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ልማት ግቦችን ለማሳካት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ ከአየር ብክለት ነፃ እና ለሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆነ ትራንስፖርትን በማስተዋወቅ እና ውብ መዳረሻዎችን በማገናኘት ዘላቂ ቱሪዝምን፣ የአከባቢ ጥበቃን እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን ይደግፋል፤ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን በመሳብ፣ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም ንገድን በማነቃቃት አከባቢው የስራ እድል ይፈጥራል ፡፡
በተጨማሪም ኮርፖሬሽናችን በአዳማ እና በሞጆ ከተሞች መካከል በሚገነባው ትልቁን የገዳ ኢኮኖሚ ዞን የባቡር መስመር ዲዛይን ፣ ግንባታ እና የማማከር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በ24ሺ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ 5 ኪ.ሜ. ርዝርመት ያለው የኢንዱስትሪ ማዕከል ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር በአገናኝ የባቡር ሀዲድ (Link rail) የማገናኘት ስራ ይከናወናል፡፡ በዚህ የኢኮኖሚ ማዕከል የሚመረቱ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በራስ አቅም በሚገነባው የባቡር አገናኝ ሀዲድ በመጠቀም ለውጭ ገበያ ምርቶችን በከፍተኛ መጠን በማመላለስ ለሀገራዊ እድገቱ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡