Ethiopian Railways Corporation

ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዘርፉን ለማሳደግ የነደፋቸውን ፕሮጀክቶች ለማከናወን ኢንቨስትመንት ለመሳብና ከአጋር አካላት ጋር ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ብሔራዊ የባቡር ቢዝነስ ኢንቨስትመንት ጉባኤ ጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ.ም በስካይላይት አካሄደ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ ባቡር ወጪ ቆጣቢ ብቻ ሳይሆን ኢንዱስትሪዎችን እርስበርስ እንዲገናኙ በማድረግ አቅማቸውን በማሳደግ ሀገራችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲኖራት የዘመነ የባቡር ስርዓትን እውን ልታደርግ ይገባል ብለዋል።

‘’ግባችን ዘላቂነት ያለው ዘመናዊ የባቡር ስርዓት መገንባት ነው::’’ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ኢንቨስተሮች በዘርፉ መሰማራት እንዲችሉ የተመቻቸ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ህሊና በላቸው (ኢ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ክልሎችን የሚያስተሳስር፣ የሀገር ውስጥ ንግድን የሚያጎለብት እና ህብረት የሚያጠናክር በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ኔትወርክ በመዘርጋት ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቀንድ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማድረግ የኮርፖሬሽኑ ራዕይ መሆኑን  ገልፀዋል፡፡

የሚገነቡ የባቡር መስመሮች የትውልድ ተስፋ እና የሀገር ብልፅግና ማሳያ በመሆናቸው ለዚህ እውን መሆን ‘’አጋርነታችንን ማጠንከር  አለብን’’  ብለዋለዋል፡፡

በቀጣይም በከባድ መኪና ማቆሚያ ግንባታ ፣ በደረቅ ወደቦች ልማት፣ ኮንሰትራክሽን እና ማማከር፣ሎጂስቲክስ፣ እና በሌሎች የንግድ ሥራዎች መሰማራቱን ጠቅሰው  ተቋሙ በኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማሩ  ተቋማት ጋር  በግል እና በመንግሥት አጋርነት ወይም በጋራ ሽርክና መንገዶች ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ባቡር የእዳ ጫና ሳይሆን ዘለቂ ኢኮኖሚ የሚያመነጭና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ማህበራዊ ትርፍ የሚያስገኝ ሀገራዊ ሀብት እንዲሆን በተናጠል ሳይሆን ጠንካራ የግልና የመንግስት አጋርነት ትስስር የሚጠይቅ በመሆኑ የአልሚዎችንና ባለሃብቶችን አጋርነት የሚሻ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ብርሃኑ ተስፋዬ (ኢ/ር) ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት በአፍሪካ ሕብረት የመሰረተ ልማትና ኢንጂነሪንግ ኮሚሽነር ሌራቶ ማታቦሜ አኅጉር አቀፍ የባቡር መሰረተ ልማት በመዘርጋት አፍሪካዊያን ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በባቡር ዘርፍ የምታከናውናቸው ስራዎች ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆንና አፍሪካ መሰረተ ልማቶቿን በራሷ ማሟላት እንደምትችል ማሳያ እንደሚሆን አንስተዋል።

 

ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ ፤
ድረ  ገፃችንንም ይጎብኙ:  www.erc.gov.et

 

 

 

 

 

 

 



Leave a Reply